ሚኒስቴሩ በግንቦት ወር ከ26 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

ሰኔ 4/2014 (ዋልታ) የገቢዎች ሚኒስቴር በግንቦት ወር ብቻ ከ26 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው አስታወቁ።

ሚኒስቴሩ ሊሰበስብ ካቀደው 27 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ውስጥ 26 ቢሊየን 902 ሚሊየን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 97 ነጥብ 23 በመቶ ማሳካት መቻሉንም ገልፀዋል፡፡

አፈጻፀሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር የብር 8 ቢሊዮን 960 ሚሊየን ወይም የ28 ነጥብ 46 በመቶ እድገት እንዳለው የገለፁት ሚኒስትሩ አፈፃፀሙ በበርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ የተመዘገበ በመሆኑ ውጤቱ እጅግ በጣም ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተሰበሰበው ገቢ ምንጭ ከሀገር ውስጥ ታክስ 13 ቢሊዮን 663 ሚሊየን ብር የሚሸፍን ሲሆን ከውጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ ደግሞ 13 ቢሊዮን 238 ሚሊየን ብር መሆኑን አመላክተዋል።

በዚህም መሰረት የአስራ አንድ ወራት 330 ቢሊዮን 980 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 309 ቢሊዮን 448 ሚሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን የ93.49 በመቶ አፈጻጸም ተመዝግቧል ነው ያሉት።

ይህ የ11 ወራት አፈጻጸም ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ከ50 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።