ሚኒስቴሩ ከ716 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በሁለት ክልሎች የሚተገበሩ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ተፈራረመ

ጥቅምት 9/2015 (ዋልታ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ716 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በሶማሌና ደቡብ ክልል የሚተገበሩ ሦስት የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ተፈራረመ፡፡

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በሱማሌ ክልል ውሃ ስራዎችና ኮንስትራክሽን ድርጅት መካከል በሁለት ፕሮጀክቶች ላይ ስምምነት ተደርጓል።

የመጀመሪያው በክልሉ ኤረር ወረዳ የሚተገበር ሲሆን ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግበትና ድርቅን መቋቋም የሚችል የ4 ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ እና ግንባታ ሥራ መሆኑ ተገልጿል።

ሌላኛው በክልሉ ቶጎጫሌ ከተማ ባለብዙ መንደር ድርቅን መቋቋም የሚችል የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ሲሆን የሲቪል ስራዎችን፣ የውሃ ቧንቧና መገጣጠሚያ እንዲሁም ኤሌክትሮሜካኒካል እቃዎች አቅርቦትና ገጠማ ሥራዎች ጨምሮ ከ490 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበት ፕሮጀክት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በእለቱ የውል ስምምነት የተደረገበት ሌላኛው ፕሮጀክት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በጌድዮ ዞን የሚተገበረው የጨለለቅቱ ከተማ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ነው።

የሲቪል፣ የውሃ ቧንቧና መገጣጠሚያ እና ኤሌክትሮሜካኒካል እቃዎች አቅርቦትና ገጠማ ሥራዎችን ጨምሮ ከ182 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግበት ተነግሯል፡፡

የፕሮጀክት ስምምነቱ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በአበበ ነጋሽ ጠቅላላ ተቋራጭ መካከል መደረጉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ስምምነቶቹን የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞና በድርጅቶቹ አመራሮች መካከል የተደረገ ሲሆን ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተግባራዊ ለማድረግ ተቋራጮቹ እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡