ሚኒስቴሩ ከሕዝብ የተነሱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን ገለጸ

ሚያዝያ 2/2014 (ዋልታ) ከሕዝብ የተነሱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለመመለስ እየሠራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በቅርቡ በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ ከሕዝብ በርካታ ጥያቄዎች መነሳታቸውን አውስተዋል፡፡

ሕዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎችም በየደረጃው ለመመለስ መንግሥት ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኑሮ ውድነት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ የውኃና መብራት መሰረተ ልማቶች ላይ ያሉ ክፍተቶችና አገልግሎት አሰጣጦች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎች ከሕዝብ መነሳታቸውን ገልጸው  በተለይ ከኑሮ ውድነት ጋር በተገናኘ የተነሱ ችግሮች በፍጥነት መፈታት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

የኑሮ ውድነቱን ችግር ለማቃለል ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠይቅም ማስታወቃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ዘይት ላይ የነበረውን እጥረት ለመፍታት ባልተለመደ መልኩ መንግሥት በቀጥታ ገብቶ ግዢ እንዲፈጸም መደረጉንም ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱንና በየወሩ የ50 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ግዢ ለመፈጸም ተወስኖ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።