ሚኒስቴሩ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር ለመስራት ስምምነት ተፈራረመ

ሰኔ 17/2013 (ዋልታ) – ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስራ እድል ፈጠራን ማበረታታትና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ማገዝ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር ተፈራረመ።

ስምምነቱ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የቆዳ ውጤቶችን በተሻለ ጥራት ለማምረትና የዘርፉን የስራ እድል ፈጠራ ለማስፋት ያለመ ነው ተብሏል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ስምምነቱ ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የስራ እድል መፍጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የዘርፉ ምሩቃን በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ስራ እንዲቀይሩ የሶስት ወራት የተግባር ስልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታም ይፈጥራል ብለዋል።

በዋናነት ስልጠና በወሰዱባቸው ኢንዱስትሪዎች የስራ እድል የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርና የተሻለ የፈጠራ ስራ ያላቸውንም በራሳቸው እንዲንቀሳቀሱ በፋይናንስ እንደሚደግፍ አክለዋል።

ስምምነቱ የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውና ለውጭ ገበያ ጭምር እንዲቀርቡ የማመቻቸት ስራዎችንም ያካትታል።

በቆዳና የቆዳ ውጤቶችም በጋራ መስራት የሚያስችለው ስምምነቱ የትምህርት ቤት ቦርሳና ጫማ በስፋት በማምረት ለተማሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋና በነጻ ለማቅረብ እየተሰራ ያለውን ስራ መደገፍም በስምምነቱ መካተቱን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በትምህርት ቤት ቦርሳና ጫማ ማምረት በመጀመሪያው ዙር 1 ሺህ የስራ እድል የሚፈጠር ሲሆን በቀጣይ ሁለት ዓመታት በሚሰሩ ስራዎችም ለ51 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል ብለዋል።

የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዓለማየሁ ኮንዴ መቀመጫውን ካናዳ ያደረገው ፋውንዴሽኑ በስራ እድል ፈጠራ ወጣቶችን በስልጠናና በፋይናንስ ለመደገፍ የተቋቋመ ግብረ ሰናይ ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል።

ብሪጅስ የተሰኘው በፋውንዴሽኑ ስር የሚተገበረው ፕሮግራም ለወጣት አፍሪካዊያን እንደ አገራቸው ሁኔታና የስራ ፖሊሲ የስራ እድል ፈጠራና ስልጠና በማመቻቸት ድህነት ቅነሳ ላይ ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።

ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር የተፈረመው ስምምነትም ምርትና ምርታማነትን በማስፋት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

እንደ አቶ አለማየሁ ገለፃ በኢትዮጵያ በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመኖራቸው የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ከፓርኮቹ ጋር የማስተሳሰር እድል ያመቻቻል።

የሚሰጣቸው ስልጠናም ከትላልቅ የማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎች ልምድ የሚያገኙበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆን ጥራት ያለው ምርት ማምረት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አክለዋል።

ፋውንዴሽኑ ከሚሰጣቸው የተግባር ስልጠና በኋላ ስራ የሚፈጥሩበት የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።

ድጋፉ ሚኒስቴሩ በመለመላቸውና ብቃታቸውን ባመነባቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚሰማሩ ወጣቶች ሲሆን በአስፈላጊ ጉዳዮች ሁሉ ትብብር እንደሚያደርጉ ዳይሬክተሩ ማስታወቃቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ስምምነቱ ሚኒስቴሩ በዘርፉ የጀመራቸውንና ሊደገፉ የሚገባቸውን ስራዎች በመደገፍና በማብቃት በዘላቂነት በጋራ መስራት የሚያስችላቸው እንደሆነም ገልጸዋል።