ሚኒስቴሩ የትምህርት ዘርፉን ብቃት ባለው የሰው ኃይል ለመገንባት እንደሚሠራ ገለጸ

ሐምሌ 4/2014 (ዋልታ) ሚኒስቴሩ ዘርፉን ብቃት ባለው የሰው ኃይል ለመገንባት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር ) ገለጹ።

ሚኒስቴሩ ለተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች በለውጥ አመራር፣ ተቋማዊ ሥነ ምግባር፣ በውሳኔ አሰጣጥ እና ተግባቦት ላይ ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡

ብርሀኑ ነጋ(ፕ/ር)በስልጠናው ላይ ባደረጉት ንግግር የትምህርት ዘርፉን ለመምራት በሙያ ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብም ብቁ መሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሠራተኞች ትውልድን የማፍራት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበው ሥራቸውን በጥራትና በብቃት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

የተሻለና ማኅበረሰቡ የሚኮራበት የትምህርት ተቋም መኖር ለሕዝብና ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ለሰራተኛውም አስፈላጊ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

ሠራተኛው የሚሠራበትን ተቋም የሚወድ፣ ሥራዎችን አክብሮ የሚሠራና ዕውቀቱንም በወረቀት ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚመዘን ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ለአራት ቀናት የሚካሄደው ስልጠና በውጭ ሀገርና በሀገር ውስጥ በትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ባላቸው ከፍተኛ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሰጠ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡