ጥር 17/2014 (ዋልታ) የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የወጣቶችን የሥራ ፈጠራ ሃሳቦች ለማበረታታት ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር የሚያከናውነው የ2014 ዓ.ም የጀነሬሽን አንሊሚትድ ለውጥ አምጪ የወጣቶች ውድድር ይፋ ሆኗል።
የውድድሩ ተልዕኮ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ወጣቶችን ከተለያዩ ዕድሎች ጋር ማገናኘት መሆኑ ተገልጿል።
በሚኒስቴሩ የአጋርነት እና ፈንድ ዳይሬክተር ጥዑመዝጊ በርሔ ወጣቶችን የማገናኘት እና አቅማቸውን የማሳደግ እንቅስቃሴ በቀድሞ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ተጀምረው በሚኒስቴሩ ከቀጠሉት አንዱ እንደሆነና ይህም ዓለም ዐቀፍ መሆኑ ይለየዋል ብለዋል።
ውድድሩ 40 በሚጠጉ አገራት መካከል የሚካሄድ፣ በኢትዮጵያ 5 ከተሞች ተከናውኖ በ8 ሳምንታት የሚጠናቀቅ፣ ሁለት ተወዳዳሪ ቡድኖችን ለዓለም ዐቀፍ ውድድር የሚያዘጋጅ፣ ለወጣቶች ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑን ገልፀው ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ዕድሉን እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።
የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ልዩ ሃሳቦቻቸውን አዳብረው የማኅበረሰባቸውን ችግር በመፍታት ተፅዕኖ ማሳደር እንዲችሉ ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።
ይህ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተዘጋጀ ውድድር የማመልከቻ መቀበያው ከጥር 17 እስከ የካቲት 1 ቀን 2014 መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
ይህንን ውድድር የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት የደገፉት ሲሆን ሥራው በፈርስት ኮንሰልት አማካኝነት ይከናወናል ተብሏል።