ሚኒስቴሩ ዲያስፖራው በቴክኖሎጂ ዘርፍ ባለው ልምድና እውቀት ሀገሩን እንዲደግፍ ጥሪ አቀረበ

ሁሪያ አሊ

ጥር 3/2014 (ዋልታ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ታላቁን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ጥሪን ተቀብለው ወደ ሀገራቸው የመጡ ዲያስፖራዎች ሀገራቸውን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል።

ሚኒስቴሩ ዲያስፖራዎች በዘርፉ ሀገራቸውን ለመደገፍ እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማየት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ በመጪው ሐሙስ ይመክራል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የግሉን ዘርፍ እና የዲያስፖራውን አባላት ተሳትፎ የሚያጠናክር ፎረም በእለቱ እንደሚመሰረት ተናግረዋል።

ዲያስፖራው ኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን ዓለም ዐቀፍ ጫና በመቃወም ያስመዘገበውን ውጤት ያደነቁት ሚኒስትር ዴኤታዋ በቴክኖሎጂው ዘርፍም ይህንን ታሪክ እንዲደግመው ጥሪ አቅርበዋል።

በመጪው ሐሙስ በሚካሄደው የምክክር መድረክ በዘርፉ ሀገራቸውን መደገፍ የሚችሉ ሁሉ እንዲሳተፉ ጥሪ መቅረቡን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።