ሚኒስትር ዴኤታዋ ከቻይና ዓለም አቀፍ የኤነርጂ ቡድን ሊቀመንበር ጋር በኢኮኖሚ ትብብር ላይ ተወያዩ

የካቲት 27/2015 (ዋልታ) የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በቻይና ዓለም አቀፍ የኤነርጂ ቡድን ሊቀመንበር በሊ ዚያንግ የተመራውን የልኡካን ቡድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው በሁለቱ አገራት መካከል በቀጣይ ስለሚከናወነው የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ትብብር ተወያይተዋል።

በውይይቱም የቻይና ዓለም አቀፍ የኤነርጂ ቡድን በኢትዮጵያ በኃይል ማመንጫና በመጠጥ ውሀ ፕሮጀክት ግንባታዎች ሲሳተፍ የቆየ ግዙፍ ካምፓኒ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያም ከካምፓኒውና ከሌሎችም የቻይና ኢንቨስተሮች ጋር ተባብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አስረድተዋል፡፡

የቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ሊቀ መንበር ሊ ዚያንግ በበኩላቸው ቡድኑ በኢትዮጵያ የተከዜ ኃይል ማመንጫን፣ የፊንጫ አመርቲ ነሽ ኃይል ማመንጫን፣ ገናሌ ዳዋ 3 ኃይል ማመንጫንና የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶችን መገንባቱን አስታውሰዋል።

ቡድኑ በቀጣይነትም በኢትዮጵያ በማዳበሪያ ፋብሪካ፣ በሲሚንቶ ፋብሪካ እንዲሁም በታዳሽ ኃይሎች ኢንቨስትምንት የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

የቻይና አለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ከቻይና ግዙፍ ካምፓኒዎች መካከል የሚጠቀስና በርካታ ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ያለው ተቋም ሲሆን ከኃይል ማመንጫ ግንባታዎች በተጨማሪ በመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች፣ በትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቤቶች ግንባታና በሌሎች በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማራ ነው ተብሏል፡፡