ማረሚያ ተቋሙ በአረንጓዴ ልማትና እንስሳት ሀብት ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ገለጸ

ሰኔ 16/2014 (ዋልታ) በአረንጓዴ ልማት፣ በእንስሳት ሀብትና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተሳተፈ መሆኑን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የማሻ ማረሚያ ተቋም አስታወቀ።

ተቋሙ አራተኛውን የአረንጓዴ አሻራ ልማት 10 ሺሕ ችግኞችን በመትከል አከናውኗል።

የማረሚያ ተቋሙ አዛዥ ኮማንደር መላኩ በቀለ ተቋሙ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የራሱን ድርሻ ለማበርከት እየሠራ ነው ብለዋል።

የሀገርን ጥሪ በመቀበልም በአረንጓዴ አሻራ ላይ በስፋት እየተሳተፍን ነው ያሉት ኮማንደር መላኩ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ከ60 ሺሕ በላይ የተመረጡ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።

ከችግኞቹ መካከልም አፕል፣ አቮካዶ፣ ቅመማ ቅመም፣ የእንስሳት መኖ እና የጥላ ዛፎች ተጠቃሾች ናቸው ተብሏል።

ታራሚዎች በማረሚያ ተቋም ቆይታቸው የተለያዩ ሙያዎችን እንዲቀስሙ በማስቻል የእስር ጊዜያቸውን አጠናቀው ሲወጡ ሥራ ፈጣሪ እንጂ ሥራ ፈላጊ እንዳይሆኑ ለማስቻል እየተሠራ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የወተት ከብቶችን በማርባት የከተማውን ነዋሪ የወተት ፍጆታ ለመሸፈን የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ልማቱ ላይ የማረሚያ ተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሠራዊት አባላት፣ ሠራተኞችና ታራሚዎች ተሳትፈዋል።

የማሻ ማረሚያ ተቋም በ1936 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም 715 ታራሚዎች አሉት።

ነስረዲን ኑሩ (ከማሻ)