ም/ጠ/ሚኒስትሩ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኀበረሰብ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለፃ አደረጉ

ደመቀ መኮንን

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኀበረሰብ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለፃ አደረጉ።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተደረጉ ጥረቶችን በስፋት ያብራሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥት ለሰብአዊ ድጋፍ ሲባል የተደረገውን የተናጥል ተኩስ አቁም ውሳኔ እና ያልተገደብ ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ለማስገባት የተደረጉ ጥረቶችን አመላክተዋል።

መንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሰላም አማራጭ ዐብይ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ሥራ መግባቱንም አስታውሰዋል።

መንግሥት የሦስተኛ ወገን ስምምነት በተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት በመፈረም እንዲሁም ከዓለም ባንክ በተገኝ ድጋፍ የአድጋ ጊዜ እና የማገገሚያ ፕሮጀክት በትግራይ ክልል ተግባራዊ እንዲደረግ መስማማቱን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ የህወሓት ቡድን መንግሥት የወሰዳቸውን የሰላም አማራጮች ወደ ጎን በመተው ጦርነት መክፈቱን እና የሚደርሰውን እርዳታም ለጦርነት እያዋለው መሆኑን ገልፀዋል።

ይህ ቡድን በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ የተጀመረውን የሰላም ጥረት በመግፋት ወደ ጦርነት መግባቱን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን ድርጊት በጽኑ እንዲያወግዝ እንዲሁም ቡድኑ ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ግፊት እንዲያደርግ መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።