ምስራቅ ኤዢያን እያወከ የሚገኘው የታይፉን አውሎ ንፋስ

በታይዋን የተከሰተው ጌሚ የተሰኘ የታይፉን አውሎ ንፋስ ምስራቅ ኤዢያን እያወከ ይገኛል፡፡ ረቡዕ እኩለ ሌሊት ላይ የተከሰተው ይህ አውሎ ነፋስ በታይዋን የሶስት ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍና በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት ምክንያት ሆኗል፡፡

ታይዋን ከ8 ሺሕ በላይ ነዋሪዎቿ የተፈናቀሉ ሲሆን ዘጠኝ ሰዎችን የጫነ የታንዛኒያ መርከብም በደቡባዊ የታይዋን ዳርቻ ላይ ሰጥሟል፡፡ አውሎ ነፋሱ ታይዋን ሁሉንም የአገር ውስጥ እና 200 ዓለም አቀፍ በረራዎችን እንድትሰርዝ አስገድዷታል፡፡

ይህ በምዕራብ የፓስፊክ ውቅያኖስ የተነሳ የታይፉን አውሎ ንፋስ ታይዋን ከመድረሱ በፊት በፊሊፒንስ ከባድ ዝናብ እንዲከሰት መንስኤ ሆኗል፡፡ አውሎ ንፋሱ ባስከተለው ከባድ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት ሳቢያም 21 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

በተጫማሪም ኤም ቲ ቴራ ኖቫ የተባለ 1.5 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ የጫነ መርከብ በፊሊፒንስ ተገልብጧል፡፡ መርከቡ ላይ የነበሩትን 16 ሰዎች ማዳን የተቻለ ሲሆን የአንድ ሰው ሕይወት ግን ማዳን አልተቻለም፡፡ በተጨማሪም ከመርከቡ ላይ እየፈሰሰ የሚገኘው ነዳጅ እጅግ አሰሳቢ ሆኗል፡፡ በአካባቢው በተፈጠረው ከባድ ንፋስና ዝናብ የመከላከል እርምጃውን በጣም ከባድ አድርጎታል፡፡ በጊዜ መቆጣጠር ካልተቻለም ከፍተኛ የስነ ምህዳር ቀውስ የሚያስከትል ነው፡፡

ይህ ጌሚ የተሰኘ የታይፉን አውሎ ነፋስ ወደ ቻይና የተዛመተ ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡ በዚህ ሰዓትም የቻይናን ደቡብ ምስራቃዊ ክፍል መምታቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ቻይና አስቀድማ 150 ሺሕ ሰዎችን ከቦታው እንዲነሱ አድርጋለች፡፡ ይሁን እንጂ አካባቢው በተደጋጋሚ በጎርፍ በመጎዳቱ አሁንም ለባሰ ጉዳት እንደሚዳርግ ተገልጿል፡፡ አውሎ ንፋሱ በቻይና ከ10 በላይ ግዛቶች ውስጥ ከባድ ዝናብ እንደሚያስከትልም ይጠበቃል ተብሏል፡፡

የጌሚ አውሎ ንፋስ ታይዋንን በ8 ዓመት ውስጥ ካጋጠሟት ታይፉኖች ጠንካራው ሲሆን በሰዓት 227 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ እንደሆነም ተገልጿል፡፡