ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ዙሪያ የጠራው ልዩ ስብሰባ እየተካሄደ ነው

ታኅሣሥ 8/2014 (ዋልታ) የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ዙሪያ የጠራው ልዩ ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡
በስዊዘርላንድ በሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎችና ሌሎች ዓለም ዐቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዘነበ ከበደ የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን ያደረጉትን የጋራ ምርመራ የናቀ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለቱ ተቋማት የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝና የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ ኃይልም ተቋቁሞ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህ ባለበት ሁኔታ ምክር ቤቱ የጋራ ጥናቱን ወደ ጎን በመተው ይሄን ስብሰባ እንዲጠራ ማድረጉ የተወሰኑ ኃይሎች የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ልዩ ስብሰባው ኢትዮጵያን የማተራመስ አጀንዳ ያለው መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ የሚተላለፉ የትኛውም ዓይነት ውሳኔዎችን እንደማትቀበል፣ እንደማትተገብርና ትብብር እንደማታደርግ አስገንዝበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡