ምክር ቤቱ በገላሳ ዲልቦ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ

መጋቢት 22/2014 (ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምክር ቤቱ አባል በሆኑት ገላሳ ዲልቦ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል፡፡
ገላሳ ዲልቦ ገና በወጣትነት ዘመናቸው ከተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ ለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት እና እኩልነት የታገሉ እና በኦሮሞ ሕዝብ የትግል ታሪክ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ጉምቱ ፖለቲከኛ እና የትግል መሪ እንደነበሩ ምክር ቤቱ በሀዘን መግለጫው አስታውሷል።
ከሦስት ዓመት በፊትም በለውጡ አመራር በተደረገላቸው ግብዣ የሰላማዊ ትግል ጉዞ መርጠው ወደ አገራቸው የተመለሱት ገላሳ በ2013ቱ ምርጫ በግል ተወዳድረው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞን የመልካ በሎ፣ ጎለ ኦዳ እና ቁምቢ ወረዳዎችን ሕዝብ በመወከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ለመሆን መብቃታቸውን መግለጫው ጠቁሟል፡፡
እንደምክር ቤቱ መግለጫ የገላሳ ዲልቦ የቀብር ሥነ ሥርዓት የፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓ.ም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል የሚፈፀም ይሆናል።