ምክር ቤቱ የሁለት ተቋማትን የቦርድ አመራሮች ሹመት መርምሮ አጸደቀ

ጥቅምት 29/2015 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 3ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን የቦርድ ሰብሳቢና አባላትን ሹመት መርምሮ አጸደቀ፡፡

የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ በልጅጌ የሁለቱንም ተቋማት እጩ የቦርድ ሰብሳቢና አባላትን ለተከበረው ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፤ እጩዎቹ ለአመራርነት ሲመለመሉ እውቀትና ዝንባሌን፣ አሳታፊነትን፣ እንዲሁም ፍላጎትና ዝግጁነትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ለሁለቱ ተቋማት የቀረቡ እጩ የቦርድ አባላትን ግለ-ታሪክ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ሚኒስትሩ፤ በትምህርት ዝግጅታቸው እና ባካበቱት የስራ ልምድ ተቋማቱን የመምራት እንዲሁም ሀገርና ሕዝብን በብቃትና በቁርጠኝነት ለማገልገል አቅም ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ለሁለቱም ተቋማት ለቦርድ ሰብሳቢነት እና አባልነት የቀረቡ እጩዎች ኢትዮጵያዊነትን የተላበሱ፣ ሀገርና ሕዝብን በብቃትና በትጋት ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ሹመቶች ወደ ምክር ቤቱ ሲመጡ በደንብ ተመርምረው ሊጸድቁ እንደሚገባ፤ ከአዋጁ ጋር የማይጣረሱ መሆን እንዳለባቸው እና የሴቶችን ተሳትፎ ከግምት ውስጥ ያስገቡ መሆን እንዳለባቸው የምክር ቤት አባላት ጠቁመዋል፡፡

የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ ለተነሱ አስተያየቶች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ የሴቶች ተሳትፎ ላይ ከቁጥር አንጻር የተነሳው ትክክል እንደሆነ እና እንደ ግብዓት የሚወሰድ መሆኑን ገልጸው በአንጻሩ በእጩነት የቀረቡት የቦርድ አመራሮች ሹመት ከአዋጁ ጋር የማይጣረስ እንደሆነ ለምክር ቤት አባላት አብራርተዋል፡፡

የተከበረው ምክር ቤት በእጩነት የቀረቡትን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢና አባላት ሹመት ውሳኔ ቁጥር 2/2015 በማድረግ በ3 ድምፀ-ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል፡፡

በተመሳሳይም ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢነትና አባልነት በእጩነት የቀረበለትን ሹመት ውሳኔ ቁጥር 3/2015 በማድረግ በ1 ድምፀ-ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

በዚህም ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፡-
1. ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት —- ሰብሳቢ
2. መሳፍንት ተፈራ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት————-አባል
3. አብዱልዋሳ አብዱላሂ (ዶ/ር) ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል— አባል
4. ታረቀኝ ቡሉልታ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ————–አባል
5. ጃፋር በድሩ ከውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት———–አባል
6. ንጉሴ ተፈራ (ዶ/ር) የሚዲያ ባለሙያ———————–አባል
7. ዩሱፍ ኢብራሂም ከአዲስ አበባ የመንግስት ንብረት አስተዳደር—አባል
8. አመለወርቅ ህዝቅኤል ከትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ባለሙያ—-አባል
9. ሙና አቡበክር (ዶ/ር) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር—–የኢቢሲ ስራ አመራር ቦርድ አባላት ሆነው ተሹመዋል፡፡
በተመሳሳይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፡-
1. ምህረት ደበበ (ዶ/ር) —– ሰብሳቢ
2. ሙሃዘ ጥበባት ዲ.ዳንኤል ክብረት —- አባል
3. ማዕረጉ በዛብህ —- አባል
4, ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) —- አባል
5. ሐና አርአያ ሥላሴ —- አባል
6. ኡስታዝ አቡበከር አህመድ —- አባል
7. መኩሪያ መካሻ —- አባል
8. ነብያ መሀመድ —- አባል
9. ካይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) —- አባል
ሆነው ተሹመዋል።