ምክር ቤቱ የኅብረተሰቡን ሐሳብ ለማድመጥ ዝግጁ ነው ሲሉ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለፁ

ታህሣሥ 12/2014 (ዋልታ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህብረተሰቡን ሃሳብ ለማድመጥ ዝግጁ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ሲቪክ ማህበራትንና ህብረተሰብን ያሳተፈ ውይይት የተካሄደ ሲሆን÷ የውይይቱን አፈፃፀም የምክር ቤቱ አመራሮች  ገምግመዋል።

በኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ከጅምሩ ይፋዊ ውይይት መደረጉ በህዝቡ ዘንድ አመኔታ እንዲኖር እና ብሄራዊ መግባባትን ለማጠናከር ድርሻው የጎላ መሆኑን አፈ ጉባኤው ገልጸዋል፡፡

አገራዊ ምክክሩ የአገሪቱን የፖለቲካ ባህሪ በመቀየር ለረጅም ጊዜ የቆየውን የፖለቲካ ችግር ሊፈታ እንደሚችል የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ተናግረዋል።

የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተደረገው ውይይት ለረቂቅ አዋጁ ጠቃሚ ግብዓት ሊሆን እንደሚችል የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ጠቁመዋል፡፡

በውይይቱ ከተሳታፊዎች የተገኘው ግብአት በፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዮስ እና በህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ ቀርቧል።

ሁለተኛው ዙር የህዝብ ውይይት ታህሳስ 16 ቀን 2014 ዓ.ም የሚደረግ መሆኑን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።