ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባሕር ዳር መግባት

መስከረም 5/2014 (ዋልታ) ለአማራ ክልል ተፈናቃዮች ድጋፍ እንደሚያደርግ የሚጠበቀው  በአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራ ልዑክ ባሕር ዳር ገባ።

ምክትል ከንቲባዋ እና ልዑካቸው በባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር እና ምክትላቸው ፈንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

አሚኮ እንደዘገበው የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ልዑካቸው ባሕር ዳር የገቡት በአሸባሪው ሕወሓት ወረራና ጥቃት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ነው።

ምክትል ከንቲባዋ በቆይታቸው ከርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ክልሉ በአሸባሪው ቡድን ወረራ በደረሰበት ጉዳት እና በዘላቂነት በሚደረጉ ድጋፎች ዙሪያ ምክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።