ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግ ገለጸች

መጋቢት 01/2013 (ዋልታ) – ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግ በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኢቨግኒ ታሪኪን ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኢቨግኒ ታሪኪንን በዛሬው ዕለት በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱም አቶ ደመቀ ቀደም ሲል ከሩስያ አቻቸው ክቡር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ያደረጓቸውን ፍሬያማ ውይይቶችን አስታውሰው፤ በቅርቡም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ም/ቤት ሰብሰባ ላይ ሩስያ ለወሰደችው መርህን መሰረት ያደረገ አቋም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሚኒስተሩ በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ለአምባሳደሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በመንግስት በኩል የሰብኣዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶችና የሚዲያ ተቋማት በክልሉ ተገኝተው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩ መሆኑን፤ የሚነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንም ለማጣራት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነግር ግን አሁንም በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነታ ያላገናዘቡ ወቀሳዎች መቀጠላቸውን አሰረድተዋቸዋል።

በተያያዘም በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታው ም/ቤት ሰብሰባ ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን ለክቡር አምባሳደሩ ገልጸውላቸዋል።

በዚህም በትግራይ ክልል የሚነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የአፍሪካ ህብረት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በጋራ ምርመራዎችን እንዲያካሂድ መንግስት ያለውን ፍላጎት መግለጹን አንስተዋል።

በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ምርመራ ለማድረግ በመንግስት በኩል ያለውን ዝግጁነት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውን አብራርተውላቸዋል።

አምባሳደር ኢቨግኒ ታሪኪንን በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የተፈረሙ ስምምነቶችን ወደ ስራ በማስገባት እንዲሁም በሂደት ያሉ ስምምነቶች እንዲፈረሙ በማድረግ በአገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ በውይይቱ መግባባት ላይ መደረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ እና ሩስያ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት አውስተው፤ በቀጣይም ሁለቱ አገራት በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን መድረኮች ያላቸውን ትብብር የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።