ራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ውጤትን ተከትሎ በፍርድ ቤት ክስ መሰረቱ

ራይላ ኦዲንጋ

ነሐሴ 16/2014 (ዋልታ) ራይላ ኦዲንጋ በቅርቡ የተካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት በመቃወም ለአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሁለት ሳምንታት በፊት ተካሂዶ በነበረው ምርጫ በጠባብ የውጤት ልዩነት በወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ መሸነፋቸው የተገለጸ ሲሆን ተቃዋሚ ፖለቲከኛው እና በወቅቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚደገፉት ራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ውጤቱ ውድቅ እና ተቀባይነት የሌለው ነው ካሉ በኋላ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።

የራይላ ኦዲንጋ ጥምር ፓርቲ የሆነው አዚሚዮ የሕግ ቡድን የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ውድቅ ለማስደረግ ለፍርድ ቤት አቤቱታውን ማቅረቡን አስታውቋል።

የኬንያ ገለልተኛ የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን ከተሰጠው አጠቃላይ ድምጽ ዊሊያም ሩቶ 50 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም ራይላ ኦዲንጋ 48 ነጥብ 8 በመቶ ማግኘታቸውን በመጥቀስ ዊሊያም ሩቶን ተመራጭ ፕሬዝዳንት ሲል ባለፈው ሳምንት አውጆ ነበር።

በአገሪቱ ሕግ መሠረት የምርጫው ውጤት ከታወቀ በኋላ ባሉት ሰባት ቀናት ተቃውሞ ያለው አካል ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታውን ማሰማት አለበት።

በዚህም መሠረት ኦዲንጋ ውጤቱን አልቀበለውም በማለት በታዋቂ የሕግ ባለሙያዎች አማካይነት አቤቱታ አቅርበዋል ነው የተባለው።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዋፉላ ቼቡካቲ ዊሊያም ሩቶን ተመራጭ ፕሬዝዳንት ብለው ያውጁ እንጂ ሁሉም የኮሚሽኑ አባላት በምርጫ ውጤቱ አለመስማማታቸውን አስታውሶ ቢቢሲ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW