ርዕሰ መሥተዳድሩ የክልሉ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል አሉ

ግንቦት 21/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) የክልሉ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ በባሕር ዳር ከተማ በተደረገው የግብርና የሜካናይዜሽን ርክክብ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የሕግ የበላይነት ከተከበረ ማንኛውም የሕዝብ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ይፈታል ብለዋል።

አርሶ አደሩ በኋላ ቀር መንገድ በመሥራቱ ጊዜውንና ገንዘቡን ሲያባክን እንደቆየ በመግለጽ የምርጥ ዘርና የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ጥገኛ መሆን የግብርናው ማነቆ መሆኑን አንስተዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ሀገር በቀል ምርቶችን መጠቀም አይነተኛ መሣሪያ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በጊዜና በእውቀትን በአግባቡ ግብርናውን ማሳደግ ይችላሉ ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

በየዓመቱ ሦስት ጊዜ ማምረት ከተቻለ ግብርናው እንደሚያድግ ገልጸው የአርሶ አደሩ አቅም የሆኑ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች መጠናከር አለባቸው ብለዋል።

ክልሉ 30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ በማድረግ የግብርና መካናይዜሽን ቁሳቁስ እያስገባ ነው።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ክልሉ 26 ሺሕ ትራክተሮችን፣ 8ሺሕ ኮንባይነሮችን ለማስገባት ማቀዱን ተጠቁሟል።

ይህም በክልሉ 500 ሺሕ ሄክታር መሬት በላይ ሜካናይዝድ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል።