ርዕሰ መስተዳድሩ ጫናዎችን የምንቋቋመው ውስጣዊ አንድነታችንን ስናጠናክር መሆኑን በተግባር አሳይተናል አሉ

ይልቃል ከፋለ

ኅዳር 9/2015 (ዋልታ) ጫናዎችን የምንቋቋመው ውስጣዊ አንድነታችንን ስናጠናክር መሆኑን በተግባር አሳይተናል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ፡፡

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ያለመ የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ሲሆን ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የአማራ ሕዝብ ከውስጥና ከውጭ በተሰነዘሩ ሴራዎች ያንዣበቡበት ፈተናዎች በሕዝቡ አንድነት ከሽፈዋል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በጠንካራ ሥራ ያመጣነውን ሰላም አጠናክረን በመቀጠል የሕዝባችንን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት መሥራት አለብን ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

አማራና ቅማንት አንድ መዓድ የሚቋደሱ፤ በማህበራዊ ትስስር የተቃኙ ሁነው ሳለ ወደ ግጭት እንዲገቡ የተደረገበት ሴራ ብዙ ዋጋ አስከፍሎን ቆይቷል ብለዋል፡፡

የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሰላም አማካሪ ምክር ቤት ተቋቁሞ ሰፊ ጥረት ተደርጎ አሁን ላይ ለደረስንበት ሰላም አድርሶናል ሲሉም አክለዋል፡፡

በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ያሳዩት ፍቅርና መተሳሰብ በአንድነት ከመኖር ውጭ ሌላ ምርጫ እንደሌለ በተግባር አሳይቶናል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ሰላም በማጣታችን ብዙ ተጎድተናል፣ ወገኖቻችን ተፈናቅለዋል፣ ከዚህ ተምረን ለሰላም ዘብ በመቆም ውስጣዊ አንድነታችንን አጠናክረን የጠላትን ዓላማ ማክሸፍ ይኖርብናል ሲሉም አሳስበዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW