ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ የዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃንን አቋም ተቹ

ኅዳር 17/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያን የተመለከተ ዘገባ የሚያሰራጩ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን የዜና ርዕሳቸውን እውነት ላይ እንዲቆም ከማድረግ ይልቅ ከሚደግፉት የሽብር ቡድኑ ሕወሓት  ጥቅም አንጻር እየቃኙ በማቅረብ ላይ መጠመዳቸውን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ መሀመድ ገለፁ፡፡

የኢትዮጵያ ሰራዊት በጦር ሜዳ ውሎው ድል ሲቀዳጅ ዓለም ዐቀፍ የተባሉ መገናኛ ብዙኃን ያለቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁምና ድርድር የሚልን አጀንዳ ያራግባሉ ነው ያሉት፡፡

በተመሳሳይ ጣልቃ ገብ አገራትም ጦርነቱ እንዲቆም አስቸኳይ ጥሪ ሲያቀርቡ ይስተዋላሉ ሲሉ ነው በፌስቡክ ገጻቸው ትዝብትና ትችታቸውን ያሰፈሩት፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ እየቀረበ ነው የሚባል ወሬ ሲሰራጭ ደግሞ እነዚያው መገናኛ ብዙኃንና አገራት በኤምባሲዎቻቸውም በኩል ጭምር ዜጎቻቸው በአስቸኳይ አዲስ አበባን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ እንደሚያስተላልፉ አክለዋል፡፡

የአሸባሪውን ሽንፈት የማይፈልጉ አካላት ሕወሓት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ሲወሰድበት ‹ግጭት አይጠቅምም፣ ምንም ዓይነት ወታደራዊ መፍትሄ የለም፣ የሰብኣዊነት ሁኔታው አሰቃቂ በመሆኑ አስቸኳይ ትኩረት ያስፈልገዋል› እና መሰል የሽብር ቡድኑን የማዳኛ ጥሪ ያቀርባሉ ሲሉ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የሴራ ዘመቻውን የተቹት፡፡