ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን ለክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሚያዝያ 15/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለብርሃነ ትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

ሕዝበ ክርስቲያኑ በፆም ወቅት ያሳየውን መልካም ተግባራትን በበዓሉም ወቅት በማጎልበት የተራቡትን በማብላት እንዲሁም የተጠሙትን በማጠጣትና ህሙማንን በመጠየቅ ወገናዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ሕዝብ በሰላም፣ በፍቅርና በአብሮነት የመኖር እሴቶች እንዲሁም በሃይማኖቶች መካከል ያለውን መቻቻልና መተባበር የበለጠ እንዲጠናከር ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሚናውን መወጣት እንደሚያስፈልግም በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አመልክተዋል።

የክልሉ መንግሥት የሕዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ እያከናወናቸው በሚገኙ ተግባራት መላው የክልሉ ነዋሪ ድጋፉን እንዲያጠናክር የጠየቁት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የህግ የበላይነትን በተሟላ ሁኔታ ለማስከበርና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሕዝቡ የበኩሉን አስተዋጾኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሰላም፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የደስታና የፍቅር እንዲሆንም ተመኝተዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!