ፍቼ-ጫምበላላ ቂም እና ቁርሾን በማስወገድ ፍቅር፣ ሰላም እና መረዳዳት የሚጎለብትበት በዓል ነው – ር/መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ርዕሰ መስተዳድር ደስታ

ሚያዝያ 17/2014 (ዋልታ) ፍቼ ጫምበላላ ወደ አዲስ ዓመት የመሸጋገሪያ የደስታ በዓል ከመሆኑ ባለፈ ቂም እና ቁርሾን በማስወገድ ፍቅር፣ ሰላም እንዲሁም መረዳዳት የሚጎለብትበት መልካም እሴት ያለው በዓል መሆኑን የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የሲዳማ ብሔር ዘመን መለዋጫ የፍቼ- ጫምበላላ በዓልን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዓሉ እሴቱን በተጠበቀ መልኩ በአደባባይ ሚያዝያ 20 እና 21/2014 ዓ.ም እንደሚከበር ገልጸው ለመላው የሲዳማ ሕዝብ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

ፍቼ ጫምበላላ ባለፋት ሁለት ዓመታት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በዓሉ በአደባባይ ሳይከበር መቆየቱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ከማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ የተመዘገበው በዓል ከሲዳማ ብሔር ሕዝብ ባሻገር የኢትዮጵያ እንዲሁም የዓለም ሕዝብ መሆኑን ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመላው ዓለም የሚገኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የሲዳማ ብሔር ወዳጅ የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆኑ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ከክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW