ሰሜን ሸዋ ዞን የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለመቆጣጠር በቅንጅት እየተሠራ ነው – የዞኑ ፖሊስ መምሪያ

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – ሰሜን ሸዋ ዞን የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለመቆጣጠር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር መከሰቱ ይታወቃል። የተደራጁ ታጣቂዎች ከሸዋሮቢት ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ዙጢ ከተማ በቅርቡ በፈጸሙት ጥቃት ሀብትና ንብረት ማውደሙን አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡
የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪዎችም የጸጥታ ስጋት እንዳለባቸው ተናግረው፣ ነገር ግን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ሸዋሮቢት ከተማ በመገኘት ነዋሪዎችን በማረጋጋት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሰርጎ ገቦች እና ተመሳስለው የሚኖሩ አካላት አሁንም የኅብረተሰቡ ስጋት መሆናቸውን አንስተዋል።
በሸዋሮቢት ከተማ ዛሬ ሱቆች፣ ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መዘጋታቸውንም ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል መንግሥትም አካባቢውን በደንብ ማደራጀትና ማኅበረሰቡ እራሱን እንዲከላከል ማድረግ እንዳለበት ጠቅሰው፣ ጥቃት በሚያደርሱ አካላት ላይ የማያዳግም ርምጃ በመውሰድም የሕዝቡን ሠላም እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር እሸቱ ጌታቸው በበኩላቸው፣ የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው የነበሩ አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይል ቁጥጥር ሥር ናቸው ብለዋል።
የመንግሥት የጸጥታ አካላትም ኅብረተሰቡን ለማረጋጋት ቅድሚያ ሰጥተው እየሠሩ መሆኑን አመላክተዋል።
አካባቢዎቹን የማረጋጋትና ወደ ነበሩበት ሠላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ እየተሠራ እንደሆነ መግለፃቸውን አብመድ ዘግቧል፡፡