ሰሜን ኮሪያ ሁለት የባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ጃፓን ባሕር አስወነጨፈች

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – ሰሜን ኮሪያ ጆ ባይደን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት የባሊስቲክ ሚሳኤሎችን በጃፓን ባህር ላይ እንደተኮሰች አሜሪካ እና ጃፓን ገለጹ።

በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት ፒዮንግያንግ አስጊ መሳሪያዎች ተደርገው የሚቆጠሩትን የባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ከመሞከር ታግዳለች።

ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ሙከራውን ያወገዙ ሲሆን፣ የአሁኑ ሙከራ ሰሜን ኮሪያ ባሊስቲክ ያልሆኑ ሁለት ሚሳኤሎችን መተኮሷ ከተዘገበ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው ተብሏል።

ጃፓን በግዛቷ ውስጥ በሚገኝ የውሃ አካል ውስጥ ምንም ስብርባሪ እንዳልተገኘ ገልጻለች።

በእስያ-ፓስፊክ አካባቢ የሚገኙ ወታደራዊ ኃይሎችን በበላይነት የሚቆጣጠረው የአሜሪካ የፓስፊክ እዝ ሙከራው “የሰሜን ኮሪያ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ መርሃ ግብር ለጎረቤቶቿ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርሰውን ሥጋት” አጉልቶ ያሳያል ብሏል።

ይህን ሙከራ ተከትሎ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያሉት ነገር የሌለ ሲሆን፣ ባይደን ከቀናት በፊት ሰሜን ኮሪያ ያከናወነችውን ባሊስቲክ ያልሆነ ሚሳኤል የማስወንጨፍ ሙከራ አሜሪካ እንደነገር ቀስቃሽ አትቆጥረውም ማለታቸውን የቢቢሲ ዘገባ አስታውሷል።

የጃፓን ባለሥልጣናት ሰሜን ኮሪያ ሁለቱን ሚሳኤሎች ሐሙስ እንዳስወነጨፈች ተናግረዋል፡፡ ከጃፓን ብቸኛ የኢኮኖሚ ቀጠና ውጭ ባሉ ውሃዎች ውስጥ ከመድረሳቸው በፊት 420 ኪ.ሜ በላይ ተጉዘው አርፈዋል። በመርከቦች ወይም በአውሮፕላኖች ላይ የደረሰ ጉዳትም እንደሌለ ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና የባይደን አስተዳደር ከሰሜን ኮሪያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማድረግ ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱን አስታውቋል።

ፕዮንግያንግ ለባይደን ፕሬዝዳንትነት እውቅና ያልሰጠች ሲሆን፣ ሁለቱ አገራት በሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር እና የባሊስቲክ ሚሳኤል መርሃግብሮች ላይ አልተግባቡም ነው የተባለው።