ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት መሆኗን አወጀች

መስከረም 2/2015 (ዋልታ) ሰሜን ኮሪያ ራሷን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት መሆኗን ይፋ የሚያደረግ ሕግ አወጀች፡፡

የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ውሳኔውን “የማይቀለበስ” ሲሉ ገልጸውታል።

ኒውክሌር ካለመታጠቅ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ድርድር ሊኖር እንደማይችልም ገልጸዋል።

በአዲሱ ሕግ መሠረት ሰሜን ኮሪያ ራሷን ለመከላከል በሚል ቀድሞ የኒውክሌር ጥቃት የመፈጸም መብት እንዳላት ይደነግጋል።

ፒዮንግያንግ በተደጋጋሚ ማዕቀብ ቢጣልባትም ከ2006 እስከ 2017 ባለው ጊዜ  ስድስት የኒውክሌር ሙከራዎችን አድርጋለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎችን በመጣስ ወታደራዊ አቅሟን ማሳደጓን ቀጥላለች።

የጦር አቅሟን በማሳደግ ከጎረቤቶቿ በተጨማሪ አሜሪካን ማጥቃት ሚያስችሉ መሣሪያዎችን ታጥቃለች።

ኪም እ.ኤ.አ. በ2019 ከወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ሁለት ዙር ንግግር ካደረጉ በኋላም የረዥም ርቀት የሚሳኤል እና የኒውክሌር ሙከራዎችን ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡