ሰራዊቱን የተቀላቀሉ ወታደሮች አቀባበል

ጳጉሜ 5/2013 (ዋልታ) መሰረታዊ የውትድርና ስልጠናቸውን አጠናቀው በወሎ ግንባር በኩል ወደ ሰራዊቱ ለተቀላቀሉ የቁርጥ ቀን ልጆች የጀግና አቀባበል ተደረገላቸው።

በአቀባበል ስነ-ሥርአቱ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የግንባሩ ከፍተኛ የጦር አዛዥ እንዳሉት ጠላት በሰራዊታችን በተወሰደበት ከፍተኛ እርምጃ እየተደመሰሰ ሲሆን፣ የወረራቸውን መሬቶች እየለቀቀ በመሸሽ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዛሬ እናንተም ለህዝባችን ድል የምታበስሩ የታሪክ ባለ አደራዎች ናችሁ ሲሉ ተናግረዋል።

የምናደርገው ጦርነት ሃገርና ህዝብን ከመበታተን የሚታደግ ፍትሃዊ ጦርነት በመሆኑ የምንጊዜም የድሉ ባለቤቶች እናንተ ናችሁ ብለዋል።

የግንባሩ ክፍለጦር አዛዥ በበኩላቸው፥ በከፍተኛ እልህና ወኔ እየተዋጋ የጠላትን ከንቱ ምኞት ካመከነ ነባር ሰራዊት ስትቀላቀሉ በዋናነት ተዋግቶ ለመሞት ሳይሆን በወታደራዊ ጥበብና ስልት እየተመራችሁ አሸባሪን ወግቶ ለማጥፋት ነው ሲሉ አሳስበዋል።

የክፍለጦሩ ምክትል አዛዥ በበኩላቸው፣ ሃገራዊ ጠላታችን የህውሓት ቡድን በሰራዊታችን መራራ ተጋድሎ ከፍተኛ ውድቀትና ኪሳራ ደርሶበት ግብአተ መሬቱ በሚፈፀምበት ወቅት ላይ ሰራዊታችንን በመቀላቀላችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።