ሰንደቅ አላማችን በትውልድ መስዋዕትነት የተገኘ የጋራ አንድነታችን ተምሳሌት ነው – ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ጥቅምት 01/2014 (ዋልታ) “በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ልዑአላዊነት ለሰንደቅ አላማችን ከፍታ” በሚል መርህ ቃል14ተኛው የሰንደቅ አላማ ቀን በዛሬው ዕለት ተከብሯል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሰንደቅ አላማችን በትውልድ መስዋትነት የተገኘ የጋራ አንድነታችን ተምሳሌት በመሆኑ በዓሉን ስናከብር ነፃ ሀገርን በደማቸው ያስረከቡንን ጀግኖች እያስታወስን የሠነቅነውን አዲስ ተስፋ እና ራዕይ እውን ለማድረግ በመትጋት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ሀገራችን በብዙ ፈተናዎች እየተፈተነች የመጣች በመሆኗ በአንድነት ከተባበርን አሁንም የገጠሙንን ፈተናዎች በድል እንወጣለን፤ ከተባበርን የማናሳከው ነገር አይኖርም ሲሉም ተናግረዋል።

ለዚህ አንድነታችን ተምሳሌት የሆነውን ሰንደቅ አላማችንን መጪው ትውልድም እንዲያከብረው እና በአግባቡ እንዲያውቀው ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሊሠራ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ሰንደቅ አላማችን የህዝባችንን  እኩልነት እና ተስፋን የያዘ በመሆኑ በዓሉ መከበሩ ፋይዳው የጎላ ነው ያሉት ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ፣  ሰንደቅ አላማችን ለአዲስ ምዕራፋችን ጅማሮ፣ ለሉአላዊነታችን ማረጋገጫ፣ ለነጋችንም ተስፋችን ነው ሲሉም አክለዋል።

በበዓሉ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ቀደምት አርበኞች የተገኙ ሲሆን፣ በዓሉ በመላው ሀገሪቱ እና የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ባሉባቸው ሀገራት እንደሚከበርም ተገልጿል።

በድልአብ ለማ