ሲሚንቶ አከፋፍላለሁ በሚል ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ በማጭበርበር የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ

ሰኔ 14/2014 (ዋልታ) ሲሚንቶ አከፋፍላለሁ በማለት ከተለያዩ ግለሰቦች ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ አጭበርብሯል በሚል ወንጀል የተጠረጠረው ግለሰብ ዛሬ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
ተጠርጣሪው በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ ሁለት የሩዋንዳ አካባቢ ነዋሪ የሆነ የ39 ዓመት ግለሰብ መሆኑ ተገልጿል።
እንደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ፣ ተጠርጣሪው “የሲሚንቶ አከፋፋይነት ሕጋዊ ፍቃድ አለኝ፣ ከተለያዩ ግለሰቦች ሲሚንቶ አቀርባለሁ” በማለት የቅድመ እና ሙሉ ክፍያ ቼክ እየሰጣቸው ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ሰብስቦ ተሰውሯል።
የግል ተበዳዮች “ቢሮ ድረስ ወስዶን ውል ፈፅመን ገንዘብ ከፍለነው ደረቅ ቼክ ቆርጦ ሰጥቶን ‘መንግሥት ሲሚንቶ ስላላስገባ ነው’ በሚል ምክንያት ሲያመላልሰን ቆይቶ ተሰወረ” በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለመያዝ ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ነው ክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ጠቅሶ ኢብኮ ዘግቧል።
የመምሪያው ምርመራ ቡድን በግለሰቡ ላይ 10 የምርመራ መዝገቦችን ያደራጀ መሆኑ እና ሌሎች በግለሰቡ ተጭበረበርን የሚሉ አቤቱታዎች እየመጡ መሆኑም ተጠቅሷል።
እንደ አቤቱታው፣ ተጠርጣሪው አጭበርብሯል የተባለው ገንዘብ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የምርመራ ሙዝገብ ያስረዳል።