ሴት ስራ ፈጣሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

ሐምሌ 15/2013(ዋልታ) – የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ከ Africa 118 ከተሰኘ በኖርዌጂያን ኤይድ ድጋፍ ከሚደረግለት ድርጅት ጋር የሴት ስራ ፈጣሪዎች በኦላይን የግብይት ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል የስምምነት ፊርማ ስነ- ስርዓት ተካሂዷል፡፡

የስምምነት ፊርማውን  የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ገ/ መስቀል ጫላ እና የ Africa 118 የሰው ሃብትና ኦፕሬሽን ዳይሬክተር

አቶ ምስጋናው አለሙ ፈርመዋል፡፡

አቶ ምስጋናው ድርጅታቸው የድረገጽ ግንባታና የዲጂታል ግብይት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመው፣ አሁን ጊዜው በኦንላይን የመገበያያ እንደመሆኑ ሴት ስራ ፈጣሪዎች በቴክኖሎጂ ታግዘው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

አቶ ገ/ መስቀል ጫላ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ የሴት ስራ ፈጣሪዎችን ለማገዝ በተለይም የገበያ ጉድለት ያለባቸውንና ቢደገፉ የተሻለ ውጤት ያመጣሉ ብለው ስለመረጡን እናመሰግናለን ብለዋል፡፡ አያይዘውም ዋናው ጉዳይ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረግ ጥረት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በመድረኩ እንደተገለጸው 500 ሴት ስራ ፈጣሪዎች የዚህ ድጋፍ ተጠቃሚ ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ 250 የሚሆኑት ከአዲስ አበባ ሲሆኑ የተቀሩት ከሌሎች ከተሞች እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡

በተጨማሪም የፋይናንስ ክህሎት ስልጠና በአካባቢው ቋንቋ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡ በዚህም ተጠቃሚ የሚሆኑት የሴት ኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት አባል የሆኑ፣ ለሌሎች የስራ እድል ሊፈጠር በሚያስችል ስራ/ ቢዝነስ የተሰማሩ እንዲሁም ድረ ገጽ ቢኖራቸው የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በፊርማው ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የሚዲያ ባለሙያዎች ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን ከፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡