ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ስለ አሸባሪው ትሕነግና የውጭ ኃይሎች

መስከረም 14/2014 (ዋልታ)  ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ጫና እያደረጉ ያሉ አገራት ፍርደ ገምድልነታቸውን እያሳዩ ነው ሲል ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ገለፀ፡፡

አሸባሪው የትሕነግ ቡድን ሥልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት ‹‹ሕጋዊ (ሥልጣን የያዘ) አሸባሪ ሆኖ በሕዝብ ላይ ግፎችን ሲፈጽም የነበረ የጨካኞች ስብስብ ነው ሲልም ከዋልታ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል፡፡

ቡድኑ አሸባሪነቱን ከሥልጣን ከተወገደም በኋላ በንፁሃን ሰዎች ላይ እየደገመ ይገኛል ብሏል።

በአሸባሪው ቡድን ተፈናቅለው በደሴና ኮምቦልቻ የተጠለሉ ወገኖችን የተመለከተው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ በሽብር ቡድኑ የተፈፀመው ድርጊት አስነዋሪና ከሰውነት ባህሪ የወጣ መሆኑን ገልጿል፡፡

አሁን ላይ በአገር ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቋቋም መተባበርና በአንድነት መቆም ይገባል ሲልም ጥሪ አቅርቧል፡፡