ሽብርተኝነትን በመከላከል የላቀ ሥራ ለሰሩ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት የማዕረግ እድገት ተሰጠ

ግንቦት 26/2014 (ዋልታ) ሽብርተኝነትን በመከላከል የላቀ ሥራ ለሰሩ 66 የሶማሊ ክልል ልዩ ኃይል አባላት የማዕረግ እድገትና እውቅና ተሰጣቸው።
በዚህም በኤልከሪ ወረዳ ለሚገኙ 66 የሶማሊ ልዩ ኃይል ሠራዊት 2ኛ ብርጌድ መኮንኖች በሶማሊ ክልል ልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል መሀመድ አህመድ መሀሙድ እውቅናና የማዕረግ እድገት ተሰጥቷል።
የክልሉና ብሎም የሀገሪቱ ሰላምና ጸጥታ የሚያናጉ አሸባሪዎች በተለይ በአልሸባብና በግብረ አበሮቹ ላይ በወሰዱት ጠንካራ እርምጃና ላሳዩት የህግ ማስከበር እንዲሁም ሥነ ምግባራቸው የማዕረግ እድገቱና እውቅናው መሰጠቱን ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል።
ለልዩ ኃይሉ አባላት የተሰጠው ማዕረግ ከምክትል ሀምሳ አለቃ እስከ ሙሉ ኮማንደርነት መሆኑም ተገልጿል።
ኮሚሽነር ጀነራል መሀመድ እውቅናና የማዕረግ እድገት የተሰጣቸው የሰራዊት አባላት በሥራቸው ባስመዘገቡት ስኬት መሆኑን ገልፀው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፋዋል።
መቀመጫቸውን በአፍዴር ዞን ኤልከሪ ወረዳ ያደረጉት የሶማሊ ክል ልዩ ኃይል 2ኛ ብርጌድ አልሸባብ እና ሌሎች አሸባሪ ኃይሎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ ሲሆን ባለፉት ወራት ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረውን በርካታ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ይታወሳል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የክልሉ ፕሬዚዳንት ጸጥታ አማካሪዎችን ጨምሮ የልዩ ኃይል አመራርና አባላት እንዲሁም የዞንና ወረዳ አመራሮች መገኘታቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።