ሽብርተኞችን ለመደምሰስ ሠራዊቱ በአስተማማኝ የዝግጁነትና ቁመና ላይ ነው

ሚያዝያ 30/2014 (ዋልታ) በምዕራብ ዕዝ የሚገኙ ኮሮች ለተከታታይ ወራት ሲያካሂዱት የነበረውን ወታደራዊ ስልጠና አጠናቅቀዋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የኮር ዋና አዛዥ ሜጀር ጄነራል ግርማ ክበበው፤ ካለፉት ውጊያዎች የተገኙ ጥንካሬዎችን ይበልጥ ለማጎልበት በተግባር የተደገፈ ወታደራዊ ስልጠናዎችን በማድረግ ተፈላጊውን አቅም መገንባት ተችሏል ብለዋል።
ወታደር እና ስልጠና የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ በመሆኑ ወታደራዊ ስልጠናው ተከታታይነት ባለው መልኩ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የ54ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ወንድሙ ነሞምሳ በበኩላቸው የጠላትን ወቅታዊ ሁኔታን ያገናዘበ እና የወገንን አቅም የበለጠ የሚያሳድግ ስልጠና ባለፉት ተከታታይ ወራት ማከናወን በመቻሉ በሠራዊቱ ዘንድ የፈጠረው አቅም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ የሚሯሯጡ የሽብር ቡድኖችን ለመደምሰስ ሠራዊቱ በአስተማማኝ የዝግጁነት ቁመና ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።