‹‹ሽንፈት ታሪካችን አይደለም›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ

                                                   ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ኅዳር 2/2014 (ዋልታ) ‹‹ባልተገባ ሁኔታ የወገንን መረጃ ጠላት እንዲያገኝ ማድረግ አይገባም። ያለንበት ጦርነት መሰረታዊ ጦርነት ጥይቱ ሳይሆን የሀሰት ወሬው ነው›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።

ጠላት ቢዋሽ የሚጠይቀው አካልም ሆነ እንዳይዋሽ የሚከለክለው የሞራል ቁመና የሌለው በመሆኑ እንዳሻው መዋሸትና የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ያሰራጫል። ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይሁንና መንግሥት በመሰል ሁኔታ ውሸትን ማሰራጨትና የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የመንዛት ፍላጎትም የሞራል ፍቃድም የለውም ብለዋል።

‹‹ሽንፈት ታሪካችን አይደለም። ኢትዮጵያዊን ወደ ሰላም መመለስ ይፈልጋሉ፤ ይህንንም ግብ አድርገን እንሰራለን›› ያሉም ሲሆን፤ ‹‹ኢትዮጵያ ጥንታዊት ብትሆንም ባለፉት 30 ዓመታት ወንድማማችነትን የሚያላላ ብዙ ሥራ ተሰርቷል። አሁን የምንሰራው ሥራም ኢትዮጵያን አለት ላይ የመገንባት ታላቅ የአገር ግንባታ ሥራ ነው›› ብለዋል።

ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ሁሉ አልፋ በፅናት ቀና ብላ የድል ታሪኳን ለሌሎችም የምታስተምር እንድትሆን በርካታ መስዋዕትነት እየከፈልን እንደኛለንም ነው ያሉት።

የአዲስ ወግ አንድ ጉዳይ ውይይት ‹‹የኅልውና ጥሪ እና አገርን የማዳን ርብርብ›› በሚል ርዕስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እየተካሄደ ይገኛል፡፡