ሽንፋንና መተማን ለመቆጣጠር የሞከረው የአሸባሪው ትህነግ ቡድን መመታት

ብርጋዴር ጀኔራል ናስር አባዲጋ

ጳጉሜ 1/2013 (ዋልታ) በቲሀ በኩል ተንቀሳቅሶ ሽንፋንና መተማን ለመቆጣጠር የሞከረው የአሸባሪው ትህነግ ቡድን በአራቱም አቅጣጫ መመታቱን ብርጋዴር ጀኔራል ናስር አባዲጋ አስታወቁ፡፡

የ8ኛ መካናይዝድ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ናስር አባዲጋ አሸባሪው የትግራይ ኃይል 11 ፓትሮል ተሽከርካሪ መኪናና 6 የቁስለኛ ማመላለሻ አምቡላንስ በቲሀ አስገብቷል ነው ያሉት።

ከቲሀ እስከ ሽንፋ ባለው መስመር አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን 1ሺህ 400 ኃይሎችን አሰልፎ እየተዋጋ ነው፤ ከዚህ መካከል 200 የሚያህሉት የቅማንት ጽንፈኛ ታጣቂዎች መሆናቸውን ጄኔራሉ ገልጸዋል።

160 የሚሆኑትም ብሬን፣ ስናይፐር፣ ክላሽና የነብስ ወከፍ ቦንብ የታጠቁ ናቸው፤ ይህ ኃይል በቲሀ በኩል ተነስቶ ሽንፋንና መተማን በመቆጣጠር ለመንቀሳቀስ ቢሞክርም በአራቱም አቅጣጫ ተመቶ ተሸንፏል ነው ያሉት ጄኔራሉ።

አሁን ላይ የተበተነው ኃይል በቲሀ ለመውጣት ሙከራ ቢያደርግም በአካባቢው ሚሊሻ መለቀሙን፤ በርካታ መሳሪያም መማረኩን፤ ጥይት መጨረሱንና በርሃብም እያለቀ መሆኑን ጄኔራሉ ገልጸዋል።

የዞኑ ማኅበረሰብ ለውጊያው እያደረገ ላለው ሁለንተናዊ ድጋፍም ጄኔራሉ ምስጋና ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።