ቀን እንዲረዝም ያደረገው ክስተት

በሳይንስ እንደተረጋገጠው ለብዙ ሺሕ ዓመታት የምድር የቀን ርዝመት ቀስ በቀስ በጥቂት ሚሊሰከንዶች በየክፍለ ዘመኑ እየጨመረ ይገኛል። ጭማሪው በአብዛኛው በጨረቃ የስበት ኃይል ምክንያት የሚፈጠር ነው።

ነገር ግን ከሰሞኑ የወጣ ጥናት የአየር ንብረት ለውጥ በምድር ላይ የቀናትን ርዝመት በፍጥነት እየቀየረ መሆኑን አረጋግጧል። ሳይንቲስቶች የዓለም ሙቀት መጨመር በፕላኔቷ ላይ አዳዲስ እና ያልተለመዱ ተጽዕኖዎችን እንደሚያሳድር በምርምር ደርሰውበታል።

አዲሱ ጥናት እንዳመላከተው የዓለም ሙቀት እየጨመረ በመምጣቱ የቀናት ርዝመትም እየጨመረ ነው። ተመራማሪዎቹ የአየር ንብረት ለውጥ በባህር ላይ የሚያስከትለውን ተፅእኖ ከመረመሩ በኋላ ከፈረንጆቹ 1900 ጀምሮ በቀን ርዝማኔ ላይ ልዩነት መፈጠሩን ተናግረዋል።

ይህ የሚሆነው በምድር ዋልታ የሚገኙ የበረዶ ንጣፍ እና ግግር ሲቀልጡ በሚፈጠረው የባህር ከፍታ መጨመር ምክንያት የቁስ አካሉ ወደ ምድር ወገብ መሰራጨት የቀኑን ርዝመት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እንዲጨምር ስለሚያደርገው ነው ተብሏል።

በአርክቲክ እና አንታርክቲካ ውስጥ ያሉ የበረዶ ንጣፍ እና የበረዶ ግግር መቅለጥ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ቁስ አካሎች ከምድር ጫፍ ወደ ምድር ወገብ እንዲጓጓዙ ያደርጋል።

በዚህም ምክንያት ሞላላው የመሬት ቅርጽ በጥቂቱ ወደ ጠፍጣፋነት እየተቀየረ እንደሚሄድ ከጥናቱ ተመራማሪዎች አንዱ የሆኑት የናሳ ጂኦፊዚስት ሰረንድራ አድሂካሪ ይናገራሉ።

ወደ ኋላ ለ3 ሺሕ ዓመታት ያህል በሚያስጉዘን መረጃ መሰረት በምድር ላይ የማያቋርጥ የቀን ርዝመት መጨመር ሁል ጊዜም ተጠባቂ ሲሆን እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የቀን ርዝመት ቀስ በቀስ ከ0.3 እስከ 1.0 ሚሊሰከንዶች የሚለካ ጭማሪ በየክፍለ ዘመኑ ሲያሳይ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ባልተለመደ መልኩ በክፍለ ዘመን እስከ 1.33 ሚሊሰከንዶች የቀን ርዝመት ጭማሪ እየተመዘገበ መሆኑን ተመራማሪው ሰረንድራ አድሂካሪ ይገልጻል። ይህ ውጤትም በዋናነት ከሙቀት መጨመር ጋር በተያያዘ የመጣ እንደሆነ በጥናቱ ተረጋግጧል።

የካርበን ጋዝ ልቀት ያለማቋረጥ በዚሁ ከቀጠለ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የቀኑ ርዝማኔ በ2.62 ሚሊሰከንድ ተጨማሪ ፍጥነት ሊያድግ እንደሚችል ተገምቷል።

እነዚህ ተጨማሪ ሚሊሰከንዶች በሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ለውጥ ባያመጡም በጊዜ መለኪያ ላይ ግን የራሳቸው ተጽዕኖ ይኖራቸዋል መባሉን ኤቢሲ ኒውስ ዘግቧል።

ሁሉን አቀፍ የሰዓት አቆጣጠር (UTC) በፈረንጆቹ 1960 የዓለም አቀፍ የጊዜ መለኪያ ተደርጓል።

ነገር ግን (UTC) በአየር ንብረት ለውጥ በተነሳው የፕላኔቷ ያልተመጣጠነ ሽክርክሪት ምክንያት አንዳንድ ከግምት ውስጥ ማስገባት የሚኖርበት ጉዳዮች እየተፈጠሩ መሆኑንም ጭምር ተመራማሪው ሰረንድራ አድሂካሪ ገልጸዋል።

የሳተላይት አሰሳ፣ ሶፍትዌር፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ ንግድ እና የጠፈር ጉዞ በUTC ጊዜ አያያዝ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው በቀን ርዝማኔ ላይ እየተመዘገቡ ያሉ ተጨማሪ ሚሊሰከንዶች የሚኖራቸው ተጽዕኖ ቀላል የማይባል መሆኑንም አስረድተዋል።