ቄራዎች ድርጅት ግማሽ በግ ለበዓል ማቅረቡን አስታወቀ

ሚያዝያ 22/2016 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ኅብረተሰቡ ለበዓል እንደየአቅሙ እንዲገበያይ ስጋዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርብ ገለጸ።

ድርጅቱ ለ2016 ዓ.ም የፋሲካ በዓል ያደረገውን ዝግጅትን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ሰው እንደአቅሙ እንዲገበያይ በማሰብ ግማሽ በግ መዘጋጀቱን ገልጿል።

በቄራ ከብት በኪሎ 570 ብር፣ ፍየል በኪሎ 510 ብር እና በግ በኪሎ 500 ብር ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ እንደሚሸጥ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሰኢድ እንድሪስ ተናግረዋል።

ለ2016 ዓ.ም የፋሲካ በዓል ከፍተኛ መጠን ያለውን እርድ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን ተናግረው በዚህም ከ7 ሺሕ 500 እስከ 8 ሺሕ እርድ ለማካሄድ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

ከግብዓት በተጨማሪ እስከ 250 ጊዜያዊ ሰራተኞች በመጨመር የአደረጃጀት ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።

ተቋሙ ከሚመለታቸው አካላት ጋር በመተባበር 241 ህገወጥ ስጋ ይዘው የተገኙ ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸው በዚህም 15 ሺሕ 295 ኪሎ ግራም ህገወጥ ስጋ ማስወገድ መቻሉን አብራርተዋል።

በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ህገወጥ እርድን በመከላከል የተጠናከረ እርምጃ እንዲሚወሰድና ለዚህም ህብረተሰቡ ህገወጥ እርድ በመጠቆምና በመከላከል የተመረመረና ጤናማ ስጋ እንዲመገብ አሳስበዋል።

በማህሌት መህዲ