ቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን በጊዜያዊነት አገደ

ሚያዝያ 28/2016 (አዲስ ዋልታ) የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ስራ አመራር ቦርድ የዋናው ቡድን ዋና አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን ከማሰልጠን ተግባራቸው በጊዜያዊነት ማገዱ ተገለጸ፡፡

የስራ አመራር ቦርዱ ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የዋናውን ቡድን እንቅስቃሴ የገመገመ ሲሆን በዚህም አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የዋናው ቡድን ዋና አሠልጣኝ እና አሠልጣኝ ውብሸት ደሳለኝ የበረኞች አሠልጣኝ ተለዋጭ መመሪያ እስኪሰጥ ድረስ ከማሰልጠን ተግባራቸው ታግደው እንዲቆዩ ወስኗል።

በምትካቸውም አሠልጣኝ ደረጀ ተስፋዬ የዋናው ቡድን ምክትል አሠልጣኝ ዋና አሠልጣኝ ሆነው ከሚያዝያ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በጊዜያዊነት እንዲያሠለጥኑ ተወስኗል፡፡

አሠልጣኝ ሳምሶን ሙሉጌታ ደግሞ የወጣት ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ምክትል አሠልጣኝ ሆነው በጊዜያዊነት እንዲያሠለጥኑ መወሰኑን ከክለቡ የማህበራዊ ትስስር ገፅ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡