ቆቦ ከተማ ወደ ቀድሞ ሠላማዊ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች መሆኗን ነዋሪዎች ገለጹ

ታኅሣሥ 19/2014 (ዋልታ) ከአሸባሪው የሕወሓት ወራሪ ኃይል ነጻ የወጣችው የቆቦ ከተማ ወደ ቀድሞ ሠላማዊ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ።

የሽብር ቡድኑ በአማራና በአፋር ክልል አካባቢዎች በቆየባቸው ጊዜያት በዜጎች ላይ ሠብዓዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔሃብታዊ ጉዳቶችን ያደረሰ ሲሆን የቆቦ ከተማም የተጠቀሱት ጉዳቶች ከደረሱባቸው አካባቢዎች መካከል ትጠቀሳለች።

እንደ ከተማዋ ነዋሪዎች ገለጻ የሽብር ቡድኑ በዚያ በቆየባቸው ጊዜያት የሴት ልጅን ኪስ ጭምር በመፈተሽ ገንዘብ እስከመቀማት የደረሰ ወንጀል ፈጽሟል።

በቤተ-እምነቶች የኃይማኖት አባቶችን በማስገደድ “በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላችሁን ተሰሚነት ተጠቅማችሁ ጥሩ ሰው ናቸው ብላችሁ መስክሩ” እያሉ ከፍተኛ ማንገላታትና ጫና ሲያደርጉም ነበር።

የሽብር ቡድኑ ወራሪዎች የኃይማኖት ተቋማት ንብረቶችን በማስወጣት ቤተ-እምነቶችን የከባድ መሳሪያ ምሽግ አድርገው መጠቀማቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የወገን ጦር በሽብር ቡድኑ ወራሪ ላይ ድል ከተቀዳጀ በኋላ ከተማዋ ወደ ቀድሞ ሠላማዊ የሥራ እንቅስቃሴ እየተመለሰች ነው ሲሉም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ የእርሻና የመኸር ሥራውን፤ ከተሜውም የንግድ ሥራውን እየከወኑ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ የሽብር ቡድኑ በከተማዋ የመንግስትና የግል ድርጅቶች ላይ ጭምር ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት ማድረሱን፤ በርካታ ዜጎችም ለሠብዓዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

ያለው ለሌለው እያካፈለ የቆየ ቢሆንም አሁን መንግስት፣ ግብረሰናይ ድርጅቶችና በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመለየት የጤና እና የሠብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎትን ጨምሮ ሱቆች ምግብ ቤቶችና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫዎች ሥራ እየጀመሩ መሆናቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።