ቋሚ ኮሚቴው ንብረቶች ከወደብ በወቅቱ እንዲነሱ አሳሰበ

ሚያዝያ 06/2014 (ዋልታ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሞጆ ደረቅ ወደብ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡

በምልከታውም ንብረቶች በወደብ ከሚቆዩበት የጊዜ ገደብ በላይ መቆየታቸው ባለንብረቶችንም ሆነ መንግሥትን ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ በመሆኑ ንብረቶች ከወደብ በወቅቱ እንዲነሱ ጠንከር ያለ የአሰራር ስርአት ሊዘረጋ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በሞጆ ደረቅ ወደብ የወደብ እና ተርሚናል ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ምህረት-አብ ተክሉ በወደቡ ያለውን የሥራ እንቅስቃሴ ሲያስረዱ በአሁኑ ሰአት በውርስ ምክንያት መሰብሰብ ካለባቸው 36 በመቶ ያህሉን ብቻ እንደሚሰበስቡ አንስተዋል፡፡

በወደቡ በአማካይ ከ3 ሺሕ በላይ ኮንቴነሮች ከ18 ቀን በላይ የሚቆዩ እንደሆኑ ነው ያስረዱት፤ በመሆኑም ከህግ ማእቀፍ አኳያ እነዚህ ከባድ ችግሮች የቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው በአዋጁ ተፈጻሚነት ዙሪያ ያለውን የድጋፍ እና ክትትል ሥራ ቋሚ ኮሚቴው በትኩረት እንደሚሰራበትም ነው የጠቆሙት፡፡

ንብረቶች በወደብ በቆዩ ቁጥር ያለ አግባብ የገንዘብ ብክነት ውስጥ እንዳይገቡ ለባለንብረቶች በማስገንዘብ እና እቃዎችን በጊዜ እንዲያነሱ አስገዳጅ ህጎችን በማሻሻል እና የተደራጀ መረጃ በማቅረብ ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡