በ130 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው የሬድ ፎክስ የመረጃ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

መስከረም 9/2015 (ዋልታ) በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ በ130 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የተገነባው የሬድ ፎክስ ሶሊሽንስ ግሩፕ የመረጃ ማዕከል እና ዋና መስሪያ ቤት በዛሬው ዕለት በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ሬድፎክስ ሶሉሽንስ የተሰኘው ኩባንያ የዛሬ አመት በፓርኩ ኢንቨስትመንት ለመጀመር የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጠ ሲሆን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የማዕከሉ ግንባታ ተጠናቆ በዛሬው እለት በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ምረቃው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሳንዶካን ደበበ፣ የሬድፎክስ ሶሉሽንስ ግሩፕ ዋና ስራ አስኪያጅ አዳነ ካሳዬን ጨምሮ የመንግስት ከፍተኛ ሀላፊዎችና የሬድፎክስ ሰራተኞ በተገኙበት ተከናውኗል።

ኩባንያው ብዙ ፈተናዎችን በማለፍ በአጭር ጊዜ ኢንቨስትመንቱን እውን ማድረጉ በዘርፉ በቂ እውቀት፣ ልምድና ፅናት ያለው ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ በመሆኑ ለኢትዮጵያ በዘርፉ ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሄ ይዞ የመጣ ስለመሆኑ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።

መንግስት ትኩረት ከሰጠባቸው አምስት ዋና ዋና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ውስጥ ዋነኛው ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሆኑን ያስታወሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው መሰል ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብና ለነባር ኢንቨስትመንቶችም የሚደረጉ ድጋፎች ሳይቋረጡ እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በ10 ኢትዮጵያውያን የተመሰረተው ሬድፎክስ በአይሲቲ ፓርክ አንድ ሄክታር የለማ መሬት በመውሰድ፣ ለ72 ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር እና 2 ሺሕ 400 ስኩዌር ካሬ የቢሮ ቦታ በመያዝ ወደ አገልግሎት ገብቷል፡፡

ሬድፎክስ በቴሌኮምና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የበርካታ አመታት ልምድና እውቀት ባላቸው እንዲሁም በተለያዩ የቢዝነስ ተቋማት በርካታ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ስራዎችንና ፕሮጀክቶችን በመሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች የተቋቋመ ነው።

አላማውም በተሟላ የመረጃ ማዕከል ግንባታ በዘርፉ የኢትዮጵያን አቅም ማሳደግ መሆኑን ይርኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡