በ2014 የክፍያ ጭማሪ ያደረጉ የግል ትምህርት ቤቶች በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉ ተገለፀ

ሚያዝያ 12/2014 (ዋልታ) በ2014 የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ ያደረጉ የግል ትምህርት ቤቶች በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉ ተገለፀ፡፡

የአዲስ አበባ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የ2015 የትምህርት ዘመንን የክፍያ ጭማሪ አስመልክቶ ከትምህርት ቤቶቹ ጋር ባደረገው ምክክር በ2014 ዓ.ም ጭማሪ ያደረጉ ትምህርት ቤቶች በ2015 የትምህርት ዘመን ምንም ዓይንት ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉ የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ህይወት ጉግሳ ተናገረዋል፡፡

ነገር ግን ላለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ጭማሪ ሳያደርጉ የቆዩ ትምህርት ቤቶች በሚያቀርቡት ፕሮፖዛል እና ከወላጅ ጋር በሚያደርጉት መግባባት መሰረት ጭማሪ ማድረግ እንደሚችሉም ተነግሯል፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፍቅርተ አበራ ከመደበኛ የአገልግሎት ክፍያ ውጭ በአይነትም ሆነ በገንዘብ ትምህርት ቤቶች ክፍያ መጠየቅ እንደማይችሉ ገልጸው ከዚህ ቀደም ያለ አግባብ ጭማሪ ያደረጉ ትምህርት ቤቶች እርምት እንዲወስዱ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፎቻቸውን ጨምሮ 2 ሺሕ የሚጠጋ የግል ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን እነዚህ ትምህርት ቤቶች 400 ሺሕ የሚጠጉ ተማሪዎችን ያስተናግዳሉ ተብሏል፡፡

ይህም ከአጠቃላይ የአዲስ አበባ የተማሪ ሽፋን 43 በመቶውን የሚይዝ መሆኑን ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW