በ3ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር 3.71 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉ ተገለጸ

3ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር

ሐምሌ 14/2013 (ዋልታ) – በሶስተኛ የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ለመትከል ከታቀደው 6 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ እስከ አሁን በሀገር ውስጥ 3.71 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን የመርኃግብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ አስታወቀ።

የአረንጓዴ አሻራ አብይ ኮሚቴ የችግኝ ተከላውን ሂደት አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጠ ሲሆን፣ ኮሚቴው የችግኝ ተከላው አበረታች ውጤት እያስገኘ እንደሆነ አመልክተዋል።

እየተተከለ ያለው ችግኝ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል እና የተሻለ ስነ ምህዳር ከመፍጠር አንፃር ከፈተኛ ፋይዳ እንዳለው ነው የሚወሳው።

ችግኝ ተከላ የጎርፍና ደለል ተጋላጭነትን ከመቀነስ አንፃርም እንደ ህዳሴ ግድብ ላሉ ፕሮጀክቶች ሚናቸው ከፍተኛ ስለመሆኑ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ ገልጸዋል፡፡

ችግኝ ተከላን የቤት ስራ አድርጋ እየሰራች ያለችው ኢትዮጵያ እስከ አሁን በ2011 እና በ2012 ዓ.ም ከተከለቻቸው 9 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ 79 ነጥብ 2 በመቶ መፅደቅ እየቻለ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የችግኝ ፅድቀት መጠን ከመጀመሪያው ተከላ ዙር በሁለተኛው የተሻለ ውጤት ተገኝቷል የተባለ ሲሆን፣ ማህበረሰቡ ችግኝን የመንከባከብ ባህሉም እየተሻሻለ እንደመጣ ተጠቅሷል።

በዘንድሮው የሶስተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር በሀገር ውስጥ ለመትከል ከታቀደው 6 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ 3 ነጥብ 71 ቢሊዮኑ እስከ አሁን እንደተተከለ አብይ ኮሚቴው ገልጿል።

ሰኔ 14 በምርጫው እለት እየመረጥን እንተክላለን በሚል መሪ ቃል 87 ሚሊየን ችግኝ መትከል እንደተቻለ የገለጸው ኮሚቴው፣ ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች በተያዘላቸው የአንድ ጀንበር መርኃግብር ተሳትፎ እያደረጉ ስለመሆናቸው ተነስቷል።

ኢትዮጵያ የወጠነችውን የአረንጓዴ አሻራ ራዕይ ለጎረቤት አገራትም የማስፋት እቅድ ይዛ እየሰራች ሲሆን፣ በዚህም ዘንድሮ በሀገር ውስጥ ለመትከል ከታቀደው ከ6 ቢሊዮን ችግኞች በተጨማሪ አንድ ቢሊዮን ችግኞች ለ10 የጎረቤት አገራት እየተከፋፈለ መሆናቸውም ተመላክቷል። ይህን ሀሳብ የሀገራቱ መሪዎች ተቀብለው እየተገበሩት ነውም ተብሏል።

በሶስተኛው ኢትዮጵያን እናልብሳት የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር መሰረት ቀሪ ችግኞችን በብሄራዊ ደረጃ በአንድ ጀንበር ለመትከል ለተያዘው እቅድ ህብረተሰቡ ዝግጁ እንዲሆንም ጥሪ ቀርቧል።

የአረንጓዴ አሻራ ዓብይ ኮሚቴ አባላትም መግለጫውን ለመገናኛ ብዙኃን ከሰጡ በኋላ የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።

(በደምሰው በነበሩ)