ኅዳር 10/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የውጭ ጫና ዘመቻ የሚያወግዝ የተቃውሞ ሰልፍ በመጪው እሁድ አሜሪካና አውሮፓን ጨምሮ ከ20 በላይ ከተሞች ላይ ሊካሄድ ነው።
ትዕይንተ ሕዝቡን በ5 አኅጉራት በሚገኙ 23 ከተሞች ለማካሄድ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ መሆኑን አስተባባሪዎቹ ለዋልታ ገልፀዋል። በዚህም ለኢትዮጵያ የተለየና አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኔትዎርክ ሊቀመንበር ማማይ ወርቁ ከአሜሪካ ከዋልታ ጋር ባደረጉት የቀጥታ የበይነመረብ ቃለመጠይቅ በእለቱ የባይደን አስተዳደር ለሃያ አመታት በአፍጋኒስታን የቆየውን ጦሩን ካስወጣ በኋላ አሜሪካን ለሌላ ጦርነት የሚጋብዝ የውጭ ፖሊሲ ነድፎ የጀመረውን የተሳሳተ እንቅስቃሴ የማውገዝ ተግባር ይከናወናል ብለዋል።
ይህን የጦርነት ነጋሪት በአሁኑ ወቅት በተለይ በኢትዮጵያ ላይ እየጎሰመ መሆኑን ለመላው ዓለም የማጋለጥና የመቃወም ስራ ይሰራል ተብሏል።
የባይደን አስተዳደር የሚያሳየውን ጣልቃ ገብነት እና ለአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቆምና የኢትዮጵያን ሉኣላዊነት እንዲያከብር የሚጠይቅ ጠንካራ ጥያቄ እንደሚቀርብም ለማወቅ ተችሏል።
ትእይንተ ሕዝቡ ከሚካሄድባቸው ከተሞች መካከል ዴንቨር፣ ካሊፎርንያ፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ደስ ሞይነስ እና ሎዋ ጥቂቶቹ ናቸው።
በነስረዲን ኑሩ