በሀላባ ዞን በጎርፍ የተወሰዱ ሰዎችን ለማግኘት እየተደረገ ያለው ፍለጋ ቀጥሏል

ሚያዝያ 28/2016 (አዲስ ዋልታ) በሀላባ ዞን ሁለት ወረዳዎች በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የአምስት ሰዎች ህይወት እንዳለፈና የሁለቱን አስክሬን ለማግኘት እየተደረገ ያለው ፍለጋ ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ገለጸ።

የሀላባ ዞን መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ሐሩና አሕመድ ለአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ እንደገለጹት ከሁለት ቀናት በፊት ሚያዝያ 26/2016 ዓ.ም በዞኑ ወይራ ድጁ እና አቶቴ ውሉ ወረዳዎች በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ የጎርፍ አደጋ ተከስቷል።

በድንገት በተፈጠረው የጎርፍ አደጋ ከአምስት ሰዎች ህይወት ማለፍ በተጨማሪ 14 ፍየሎች መሞታቸውንና 30 ሄክታር ላይ የለማው ሰብል መውደሙን አመላክተዋል።

በተጨማሪም በቁሊቶ ከተማ በሚገኘው አጠቃላይ ሆስፒታል ጎርፍ በመግባት በህክምና መሳሪያዎች ላይ ባደረሰው ጉዳት በአገልግሎቱ ላይ መስተጓጎል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ህይወት ካለፈባቸው አምስት ሰዎች ሦስቱ ልጆች ሲሆኑ ከ7 እስከ 12 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እንደሆኑ ያመላከቱት ኃላፊው የሁለቱ ሰዎች አስክሬን እስካሁን አለመገኘቱን ጠቁመዋል።

አስክሬናቸውን ለማግኘት የፖሊስ አባላትን ጨምሮ የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝና ጎርፉ ወደ ሻላ ሀይቅ የሚገባ በመሆኑ በሀይቁ ላይ ፍለጋው እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ በፊት በአካባቢው ጎርፍ የሚፈጠር ቢሆንም በሰው ህይወት ላይ ያደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ያስታወሱት ኃላፊው በቀጣይ መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ በትኩረት በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ ጊዜው የዝናብ ወቅት በመሆኑ ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በመጪዎቹ ቀናት ከፍተኛ መጠን ያለው የዝናብ ስርጭት ስለሚኖር ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡

ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የምዘንበው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የተለያዩ ዓይነት ጉዳቶች እየደረሱ መሆናቸውን ያገኘናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

በአድማሱ አራጋው