በሀረሪ ከ2 ሺሕ ሊትር በላይ ነዳጅ በቁጥጥር ስር ዋለ

ሰኔ 17/2014 (ዋልታ) ከሀረሪ ክልል በህገወጥ መንገድ ሊወጣ የነበረ 2 ሺሕ 879 ሊትር ነዳጅ በቁጥጥር ስር መዋሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ነስሪ ዘካሪያ እንደገለፁት ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 2 ሺሕ 879 ሊትር ነዳጅ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ነዳጁን በህገወጥ መንገድ ሲያንቀሳቅሱ የነበሩ አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በህገወጥ መንገድ ከክልሉ ሊወጣ የነበረ 100 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
ኮሚሽኑ የክልሉ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ የሚያደርጉ አካላትን የመቆጣጠርና የመከላከል ሥራን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ኮሚሽኑ ህገወጥ ተግባራትን ለመከላከል እያከናወነ ባለው ተግባር ኅብረተሰቡ እያደረገ የሚገኘው ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)