በሀረሪ ክልል 17ኛው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው

ኅዳር 9/2015 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል 17ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በዓል በተለያዩ ኩነቶች እየተከበረ መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ አሪፍ መሀመድ ገለጹ፡፡

ምክትል አፈጉባኤው አሪፍ መሀመድ በዓሉን አስመልክተው እንደተናገሩት በየዓመቱ ኅዳር 29 የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል የህዝቦችን አንድነትን እኩልነትን ከማጎልበትና የፌዴራል ሥርዓቱን ከማጠናከር አንፃር ጉልህ ድርሻ አለው።

ዘንድሮ ለ17ኛ ጊዜ የሚከበረው በዓልም በክልሉ በተለያዩ ኩነቶች እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።

በክልል ደረጃ በዓሉ አከባበር የተሳካ ሁኔታ እንዲከበር እቅድ ተዘጋጅቶ እና ኮሚቴዎች ተቋቁመው የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመው በአሁኑ በዓሉ በተለያዩ ኩነቶች እየተከበረ ነው ብለዋል።

በዓሉ በተለይም በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነትና እኩልነት በሚያጠናክርና ህብረ ብሄራዊነትን በሚያጎለብት መልኩ እየተከበረ መሆኑን አብራርተዋል።

በዓሉ በፓናል ውይይቶች፣ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ በጽዳት ዘመቻ፣ የአርሶ አደሩን ሰብል በመሰብሰብና በሌሎች መርኃ ግብሮች እየተከበረ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

በቀጣይም ከአጎራባች ክልልችን ባሳተፈ መልኩ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

የዘንድሮው በዓል በመንግስትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት በተደረገበት ማግስት መከበሩ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቁመው በዓሉ ሲከበር ዘላቂ ሰላምና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ማክበር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ እየተከበረ የሚገኘው 17ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀን ኅዳር 24/2015 ዓ.ም ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ተጠቁሟል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር ቅርንጫፍ)