በሀረሪ ክልል ለሚገኙ የሚዲያ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው

ኅዳር 25/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በክልሉ ለሚገኙ የሚዲያ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሀረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሄኖክ ሙሉነህ በክልሉ የሚገኙ የሚዲያ ባለሙያዎች ወቅቱን ያገናዘበ እና የሕዝብን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ሊያጎለብቱ እንዲሁም የኅብረተሰቡን አብሮነትና አንድነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ ተግባራት ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ አሸባሪው ሕወሓትና ሸኔ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር እያከናወኑት ሚገኘውን ሀገር የማፍረስ እንቅስቃሴን ከመመከት አንፃር ሕዝቡ እያደረገ የሚገኘው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያጠናክር በትኩረት መስራት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የምዕራባውያን ሚዲያዎች እያዘራጩት የሚገኙ የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን ከመከላከል አንፃር የሚዲያ አካላት ሚና የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከአቅም ግንባታ ስልጠናው ጋር ተይያዞም ሀረማያ ዩኒቨርስቲ ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ላደረገው የበጀት ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ቀጣይም የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ዘርፉን ለማሳደግ መሰል የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እንሰጣለን ብለዋል፡፡
ስልጠና ከመስጠት ባለፈም ኅብረተሰቡን የመረጃ ባለቤት ለማድረግና የሚዲያና ህዝብ ግንኝነት ባለሙያዎችን የመደገፍና የመምራት ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በልማታዊ ጋዜጠኝነትና በሚዲያ ልማት ላይ ትኩረቱን ባደረገው ለሁለት ቀናት በሚሰጠው ስልጠናም ከኦቢኤን፣ ሀረር ብዙኃን መገናኛ ኤጀንሲ፣ ሀረማያ ፋና ኤፍ ኤም፣ ኢዜአ እና ከመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተውጣጡ ጋዜጠኞች እየተሳተፉ መሆኑን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።