በሀረሪ ክልል ልዩ የወጪ ቅነሳና ቁጠባ አጠቃቀም መመሪያ ወጣ

መስከረም 4/2015 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ በ2015 በጀት ዓመት የሚተገበር ልዩ የወጪ ቅነሳና ቁጠባ አጠቃቀም አዲስ መመሪያ ማውጣቱን አስታወቀ።

አዲሱ መመሪያ የወጣው የክልሉ ካቢኔ በ2015 በጀት አመት ወጪን በመቀነስ፣ ገቢን በመጨመር እና ሀብትን በቁጠባ ለመጠቀም እንዲቻል የስራ ማስኬጃ በጀትን በ16 በመቶ እንዲቀንስ በሰጠው አቅጣጫ መሰረት መሆኑም ተገልጿል።

መመሪያው በክልሉ ለበጀት ዓመቱ የተመደበው በጀት ወጪን በመቀነስና በመቆጠብ ስራ ላይ ለማዋል እና የሃብት ብክነትን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ቢሮው ገልጿል።

ለተግባራዊነቱ በየደረጃው ያለው አመራር በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንደሚገባው እና ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይም እርምጃ እንደሚወሰድ ቢሮው አስታውቋል፡፡

የክልሉ ካቢኔ ለበጀት ዓመቱ ከተመደበው በጀት ውስጥ 51 በመቶው ለካፒታል እንዲሁም 49 በመቶው ለመደበኛ በጀት እንዲውል መወሰኑን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ጠቁሟል፡፡