በሀረሪ ክልል በ224 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ

ሰኔ 15/2016 (አዲስ ዋልታ) በሀረሪ ክልል በ224 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ኦርዲን በድሪ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

ከክልሉ አጠቃላይ በጀት 57 በመቶውን ለካፒታል በጀት በመመደብ በተለይም የንፁሃን መጠጥ ውሃ ችግርን ለመቅረፍ የላቀ ትኩረት በመስጠት ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል።

በእለቱ የተመረቀው ፕሮጀክት የክልሉን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን በማቃለል ረገድ ጉልህ ሚና ያበረክታል ሲሉም ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት የመጠጥ ውሃ ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የሃይል አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ እና የአካባቢው ጥበቃ ስራዎች ትኩረት መስጠት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ዲኒ ረመዳን በበኩላቸው በአሁን ወቅት በቀን ወደ ከተማው የሚገባው ነባር የውሃ ምርት ከ2 ሺሕ 500 ሜትር ኩብ መሆኑን ጠቁመው ፕሮጀክቱ ይህንን ወደ 7 ሺሕ ሜትር ኩብ ያሳድጋል ብለዋል።

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከውጭ የመጡ የክልሉ ተወላጆችና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)